top of page

መለያየት ሞት ነው « ት ሞ ታ ለ ህ ! »

Updated: May 6

ዓለማየሁ ገላጋይ፣

መለያየት ሞት ነው»፣


በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ-ልደት እና በዓለ-ጥምቀት መካከል እንገኛለን፡፡ ቀጥሎም ጥምቀቱን ስቅለት፣ ስቅለቱን ሞት፣ ሞቱን ትንሣዔ ይከተሏቸዋል፡፡

ዛሬ ይሄን ሰበብ አድርገን መለኮታዊውን ሳይሆን ምድራዊውን ሞት እናትታለን፡፡ በተለይም ትንሳዔና ስርየት የሌለበትን ፖለቲካ ሰራሹን «ዘንጋኤ-ሞት» እናወሳለን፡፡

ሰውን ከክፋት፣ ከስስት፣ ከትዕቢት፣ ከዕብሪት… ጋር የሚያፋቅረው የመጀመሪያው ምክንያት ዝንጋኤ-ሞት እንደሆን በአመዛኙ ያስማማል፡፡ ከነተረቱ «ሞትን ማሰብ፣ ከሁሉ መሰብሰብ» ይባላል፡፡

«ሞትን ያህል ዕዳ፣ መቃብርን ያህል እንግዳ» መዘንጋት ሰው በሀብቱና በጉልበቱ ፈፅሞ እንዲመካ ይገፋፋዋል፤ ማን-አህሎኝነት ይወርሰዋል፡፡
ይሄንን ከመሠረቱ የተረዱ ጥንታዊዎቹ ሮማውያን ለገዢዎቻቸውና ለጀግኖቻቸው አንድ አዛውንት ይመድቡ ነበር አሉ፡፡ ገዢው ማለዳ ተነስቶ ቁርስ ሲቆርስ ያ አዛውንት ድንገት ዘው ብሎ በመግባት አንዲት ቃል ብቻ ተናግሮ ይወጣል፡-
«ትሞታለህ!»
ሮማዊው ጄነራል ከድል መልስ በሰረገላ ሆኖ ወደ ከተማው ሲመለስ ህዝቡ ዘንባባ ይዞ በክብር ይቀበለዋል፡፡ ምርኮውና ግዳዩ እየተግተለተለ በፊቱ ሲያልፍ በዚህ ደስታ መካከል ያ አዛውንት ከጄኔራሉ ጀርባ መጥቶ ያንኑ ቃል አንዴ ተናግሮ ይመለሳል፡-
«ትሞታለህ!»
ሞትን ማሰብ የመታበይ መድህን ነው፡፡ የመታበይ ብቻ ሳይሆን የማግበስበስ ፍቱን መድኃኒት ነው፡፡ «ሞትን በማሰብ ከሁሉ መሰብሰብ» የቻለ ገዢ በማጣት እዚህ አገርና ሕዝብ ይቃትታሉ፡፡
«ሁሉን አንቋሻሽ፣ የተገኘውን አግበስባሽ» በሆኑ መሪዎች ፈቃድ ላይ ዕጣ-ፈንታችን ወድቋል፡፡ አንድ ሰው መብቱ እስከ መገንጠል ቢፀናለት ከኤርትራ የማያንስ ሀገር መሆን የሚያስችለውን መሬትና ሀብት በስርቆት እንደሰበሰበ መስማት የተለመደ ነገር ሆኗል፡፡
አጤ ምኒልክ አገር-ረግቶ በተረጋጉበት ዘመን የግል መሬት እንዲይዙ ተመከሩ አሉ፡፡ እንዲህ ሲሉ ምላሽ ሰጡ፡- «መላው ኢትዮጵያ የማን ሆነና እኔ በግሌ መሬት እይዛለሁ?» ስለዚህም በስማቸው የተያዘ አንድም መሬት አልነበረም፡፡
እንደውም የእናታቸውን የዘር ርስት ወራሽ እንደሆኑ ቢታወቅም መቴሩን በባለቤትነት ተቆጣጥረው አያውቁም፡፡ ታዲያ አንድ ጊዜ መሬቱን የሚያርሰው ገበሬ ከምስለኔው ጋር በግብር ተጣልቶ ምኒልክ ፊት ሲቀርብ እንዲህ አሉ፡-
«ፈጣሪዬ የመላ ኢትዮጵያ አባት
ስላደረገኝ እሱም (ገበሬው) ከልጆቼ
አንዱ ነውና በስሙ ሊገብር ይችላል፡፡»
አጤ ምኒልክን ለዚህ «በቃኝ ባይነት» ያበቃቸው አዘውትወረው ሞትን ማሰባቸው ነበር፡፡ የአድዋ ድል 7ኛ ዓመት ሲከበር ለየመኳንንቱና ለየጭፍራው በጻፉት ደብዳቤ ላይ ይኸው ሞትን አለመዘንጋት በጉልህ ይታያል፡፡
«… በዚህ በየሥራው ነገር በእንጨት
በድንጋይ የደከማችሁን አትመልከቱ፤
ይልቅ እኔን ስታጡ ብርቱ ሀዘን ያገኛችኋል፡፡»
ይላሉ፡፡ እንደ ሮማዎቹ ቄሳሮች «ትሞታለህ!» የሚል አስታዋሽ ሳይመደብባቸው «እሞታለሁ!» ያሉ ታላቅ መሪ ናቸው - አጤ ምኒልክ፡፡
ከዚያ ጊዜ ወዲህ ነገር እየተበላሸ የመጣ ይመስላል፡፡ በሞት ፈንታ ዘላለማዊነት የነገሰበት የገዢ ልብ «የላይ ሰፈር» ሰዎቻችንን ተጠናወተ፡፡ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የነበሩ ተማሪዎች እንዲህ ሲሉ በቅኔ ንጉሡን አንጓጠው ነበር፡-
«ዛሬስ አቶ ኃይሌ አረጀ-ደቀቀ፣
ምድር ይይዝ ጀመር እየተንፏቀቀ፤»
ይኸው «የጠሉት ይወርሳል፣ የፈሩት ይደርሳል» ሆነና ከራሳቸው ከተማሪዎቹ መካከል የወጡት ጓዶቻቸው ዛሬ «ንጉሥ» ሆነው «እየተንፏቀቁ ምድር በመያዝ» ከአፄ ኃይለሥላሴ ብሰው ተገኙ፡፡ ይሄን ጉድ ተማሪዎቹ ቢያዩ ምን ይሉ ነበር ይሆን?
ለመሆኑ «ለአንድ ሰው ስንት መሬት ይበቃዋል?» ይሄን የጠየኩት እኔ አይደለሁም፡፡ ሞት እንዳለ ገብቶት እርስቱን ለጭሰኞች በማከፋፈል ሙልጩን የቀረው ታላቁ ሩሲያዊ ደራሲ ልዮ ቶልስቶይ ነው፡፡ «አንድ ሰው ስንት መሬት ይበቃዋል?» ቶልስቶይ የጻፈው ተረት ርዕስ ነው፡፡
ሰውየው ልክ-የለሽ የመሬት ጥማቱን ለማርካት ወደ አካባቢው አዛውንቶች ይሄዳል፡፡ በመሃከላቸውም አንድ ስምምነት ያደርጋሉ፡፡ ፀሐይ ወጥታ እስክትገባ በሩጫ መሸፈን የሚችለውን መሬት ሁሉ እንደሚወስድ፣ ይህ የሚሆነው ግን ጀንበር ከመጥለቋ በፊት ማለዳ የተነሳበት ቦታ ላይ መድረስ ሲችል ብቻ ይሆናል፡፡
ሰውየው «በደስታ» ብሎ ሩጫ ይጀምራል፡፡ ይሮጥ ይሮጥና «ይሄ ለስንዴዬ» ይላል፡፡ አሁንም ይሮጥ ይሮጥና «ይሄ ለገብሴ» ይላል፡፡ ሩጫውን በመቀጠል «ይሄ ለበቆሎዬ» … ቀና ሲል እየመሸ ነው፡፡ ወደተነሳበት ተመልሶ መሮጥ ይጀምራል፡፡
በመጨረሻ እቦታው ላይ ሲደርስ ግን ሰውየው ልቡ ፈንድቶ ይሞታል፡፡ ቶልስቶይም በአንዱ ገፀ-ባሀርይ በኩል «ቅበሩት» ይላል፡፡ ለአንድ ሰው የሚበቃው መሬት የቁመቱን ያህል የሚቀበርበት ብቻ ነው፡፡
የእኛዎቹ ባለሥልጣናት ፀሎታቸው ሰምሮ የከተማ መሬት በመሰብሰብ ላይ ናቸው፡፡ የፎቅ ማሳ እያለሙ «ይሄ ለሚስቴ፣ ይሄ ለሚስቴ እህት፣ ይሄ ለልጄ፣ ይሄ…» ሲሉ «በሩጫ» ልባቸው ፈንድቶ መሞታቸውን ዘንግተውታል፡፡
ሞትን በሥልጣን እንቅልፍ ተላምደውት ከመሀከላቸው ጓዳቸው ሲነጠቅ እንኳ የማይበረግጉ ልበ-ደንዳና ሆነዋል፡፡ ይሄ ልበ-ደንዳናነታቸው «ምን ያመጣብን ይሆን?» የሚያሰኝ ስጋት ይተክላል፡፡
እንደ አጤ ምኒልክ፣ ያለ-ቀስቃሽ መንቃቱ ይቅር፣ እንዴት በራሱ፣ በባለቤቱ (በሞት) የተወረወረ ፍላፃ እኩዮቻቸቸው ላይ ሲያርፍ መባተት ሳይኖር ቀረ? ለማንኛውም እንደ ጥንታዊዎቹ ሮማዎች እኛም ቄሳሮቻችንን «ትሞታለህ!!» በማለት እንትጋ፡-
«መሬት ሰበሰብክ? ትሞታለህ!!»
«ሀብት አጋበስክ? ትሞታለህ!!»
«ልብህን አደነደንክ? ትሞታለህ!!»
የብሉይ ኪዳኑ የአማሌቅ ንጉሥ አጋግ በሌከሎች ሞት ላይ ልበ-ደንዳና ነበር፡፡ ሠይፉ ሴቶን ሁሉ ልጅ-አልባ ሲያደርግ ሞት ለእርሱ ተራ ነገር ነበር፡፡ ይሁንና ቀኑ ደርሶ እርሱም በተራው ነብዩ ሳሙኤል እጅ ላይ ሲወድቅ ተንቀጠቀጠ፡፡
«ሠይፍህ ሴቶችን ልጆች-አልባ
እንዳደረጋቸው እንዲሁ እናትህ
በሴቶች መካከል ልጅ-አልባ ትሆናለች»
አለ ነብዩ ሳሙኤል፡፡ ይሄን ጊዜ አጋግ «በእውኑ ሞት እንደዚህ መራር ነው?» ሲል እራሱን ጠየቀ፡፡ አጋግ ለገደላቸው፣ ሞት እንዲያ ከባድ እንደሚሆን እነዴት ሳይረዳ ቀረ? ልቡን ምን አደነደነው? መግደል በመገደል እንደሚጠናቀቅ ሳይገለፅለትስ እንዴት ቀረ? …
አጋግን አልን እንጂ እኛስ ጋ እንዲሁ አይደል? ሞትን ከመሞት በፊት ማሰብ ለዚህች አገር ገዢዎች እንግዳ ነገር ነው፡፡ ከአጤ ምኒልክ በተጨማሪ ሞትን አሳቢ ንጉሥ ሆነው ያገኘኋቸው አጤ ቴዎድሮስን ነው፡፡ ይቺን ታሪካቸውን እንመልከት፡-
አጤ ቴዎድሮስ የጎንደርን ሊቃውንት ሰብስበው እንዲህ ሲሉ ጠየቁ ይባላል፡-
«ጌታ ቀድሞ ዓለምን ፈጠረ፤ በኋላ
አምላክነቱን ለማሳወቅ የበኸር ልጅ
እያለ እያቆላመጠ ዘመነ አበውን፣
መሳፍንትን፣ ነገሥታትን አሳለፈ፡፡
በኋላም ለእኛ ብሎ ከሠማየ-ሠማያት
ወርዶ፣ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፣
ሰላሣ ሦስት ዓመት ኢየሩሳሌምን ዙሮ፣
ተገፎ፣ ተገርፎ፣ ሞቶ፣ ተነስቶ እኛን አዳነ፡፡
ይኸን ሁሉ ሥራውን ከፈፀመ በኋላ
ተመልሶ ወደ ሠማይ አረገ፡፡ ከዚህ ሁሉ
ወዲያ እዚያ ምን ይሠራል?»
በአጤው ጥያቄ ሊቃውንቱ ሁሉ ተጨነቁ፡፡ «ምን ብንል ይሻላል?» እያሉ ሲያወጡ ሲያወርዱ አንድ ዓይነ-ሥውር «እኔ ልመልስ ጃንሆይ?» አሉ፡፡
«እስኪ መልስ ቆማጤ ቆመጥማጤ» አሉ ንጉሡ፡፡
«ንጉሥ ሆይ፣ ቁና ይሰፋል» አላቸው፡፡
«እውነቱን ነው ይሄ ምናምንቴ፤
አግኝቶታል፡፡ ወይኔ መይሳው!
ይህን ጊዜ ባይሞላለት ነው እንጂ
የእኔንም ቁና እየሰፋ ነው»
ብለው መላሹን ሸልመው ሰደዱት፡፡ ቁናው በሞት እጅ የሚላክልን የብድራት መስፈሪያ መሆኑ ነው፡፡ አጤ ቴዎድሮስ «የእኔንም ቁና» ያሉት የተቀጠበችውን የዕለት-ሞት ቀንን ነው፡፡ ምነው ያሁኖቹ አጤዎች ከዚህ ቢማሩ? እስኪማሩ ግን እኛ ዝም አንልም «ትሞታለህ!!» እንላቸዋለን፡፡
«በወታደር ተከበብክ? ትሞታለህ!!»
«ጥይት በማይበሳው መኪና ሄድክ? ትሞታለህ!!»
«አዘዝክ? ናዘዝክ? ትሞታለህ!!»
«በውጭ አገር ገንዘብ አካበትክ? ትሞታለህ!!»
«40 ዓመት እንገዛለን አልክ? ትሞታለህ!!»
«የሞተ [ሥርዓት] አስቀጥላለሁ አልክ? ትሞታለህ!!»
«ትሞታለህ! ትሞታለህ! ትሞታለህ! …»
♤♡◇♧♤♡◇♧♤♡◇♧♤♡◇♧
ዓለማየሁ ገላጋይ፣ «መለያየት ሞት ነው»፣
ገጽ 32-35

Comments


bottom of page