የቼክ ሪፐብሊኩ ተወላጅ ደራሲ አዶልፍ ፓርለሳክ ተጽፎ በተጫነ ጆብሬ እንደተተረጎመው
“…ነጩ ጎርፍ የወደቀውን የጦር ሜዳ ጓዱን እየዘለለ ወደፊት ይነጉዳል ። አንድ ሲወድቅ ሌሎች አስሮች እየተተኩ፣ አስሮች ሲወድቁ ሌሎች ኅምሳዎች እየተተኩ የጣልያንን ጦር እንደ ደራሽ ውሃ አጥለቀለቁት ።
የኢትዮጵያ ሰራዊት ከጎኑና ከፊቱ የሚወድቀውንና የሚረግፈውን ወንድሙን እየዘለለ ሲጓዝ ከላይ ከተራራው ጫፍ ላይ ደግሞ በሺ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ተዋጊዎች ድንጋዩን እየዘለሉ፣ እየፎከሩና እየሸለሉ ወርደው ተቀላቀሉ፡፡ ራስ ካሳ የማያልቀውን የሰራዊት ጎርፍ ሲመለከቱ ፈገግ ብለው ወደኔ በመዞር 'አየህ ጌታው ኢትዮጵያዊ እንዲህ ነው የሚዋጋው' አሉኝ፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሲወለድ ጀምሮ ጀግና ተዋጊ ነው፣ አንዴ ውጊያ ውስጥ ከገባ በምድር ላይ የሚያቆመው ኃይል የለም አሉኝ፡፡ ደግሞም ከታች ባለው ጦር ሜዳ የኢትዮጵያ ወታደር በጦር የጠላቱን ደረት እየሰነጠቀ በጎራዴው አንገት ሲቀላ አሳዩኝ፡፡...
ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ግን ድል በጃቸው ገብቶ የነበሩ ኢትዮጵያውያን በ3 ታንኮች የሚረቱ መሰለ፡፡ እንዲህ ድል ወደ ጣሊያኖች ባዘነበለበት ሰአት አንድ ሽማግሌ ፊቱን አዙሮ ወደ ታንኮቹ ሲሮጥ አየሁ፡፡ መጀመሪያ ላይ ወደ 100 የሚጠጉ፣ ቀጥሎም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሽማግሌውን ተከተሉት፡፡ የኢጣሊያ ታንኮች የፊተኛውን ረድፍ ኢትዮጵያውያን እያጨዱ ማስተኛታቸውን ቀጠሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን የጀግኖቻቸው ሬሳ ቢከመርም ወደ ኋላ ሳይሆን አሁንም የወደቁ ጀግኖቻቸውን ሬሳ እየዘለሉ ወደ ፊት ገፉ፡፡
አሁን አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ወደ ታንኮቹ በጣም ተጠግተው አነጣጥረው ለመተኮስ ቢሞክሩም ብረት ለበሶቹ ታንኮች ያለምንም ርህራሄ በጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ላይ እየወጡባቸው ወደ ፊት ገሰገሱ፡፡ በዚህ መሀል ግነ የተንቤን ሙቀት ታንከኞቹን የላይኛውን መግቢያ በር እንዲከፍቱ አስገደዳቸው፡፡
ይህንን ሰፊ ቀዳዳ ያዩት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ጦራቸውን ሰብቀው በመሄድ ላይ ባለው ታንክ እየቧጠጡ ወጥተው ወደ ታንኩ ውስጥ ጓዳ መወርወር ጀመሩ፡፡ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የመጀመሪያዋ ታንክ ድምጹዋን አጥፍታ ቆመች፡፡የመጀመሪያዋን ታንክ እጣ ፈንታ ያዩት ቀሪዎቹ 2 ታንኮች ፊታቸውን አዙረው ወደ ጦር ሰፈራቸው መፈርጠጥ ጀመሩ፡፡
በሽሽት ላይ ካሉት 2 ታንኮች አንዷ የተንቤን አሸዋማ መሬት ከድቷት ስታጓራ በርካታ ነጭ ሸማ ለባሽ ኢትዮጵያውያን በታንኳ አናት ላይ ወጥተው ጦራቸውን ሰብቀው ሲወረወሩ ታንኳ እየየዋን አቁማ ጸጥ አለች፡፡ 3ኛዋ ታንክ አመለጠች፡፡ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች 1 ሰአት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በባዶ እጅ፣ በጦርና በጎራዴ 2 በዘመኑ አሉ የተባሉ ዘመናዊ ታንኮችን በመማረክ በእጃቸው አስገቡ ።…”
******
የሃበሻ ጀብዱ መጽሐፍ ገፅ 173-177
በአዶልፍ ፓርለሳክ ተጽፎ በተጫነ ጆብሬ እንደተተረጎመው
Comments