top of page

ወሪሳ

አለማየሁ ገላጋይ

ተማፅኖ

"በቅሎ ማሰሪያዋን በጠሰች ለገዛ እራሷ አሳጠረች" ነው። እንግዲህ ማሰሪያዬን በገዛ እራሴ አሳጥሬአለሁ። እምጰርጵር ቀድሞ የነበረኝን ነፃነት አይሰጡኝም። ቀልቤ ይቀንሳል፥ ቋጠሮዬ ይጠባል... በተቀናነሰ ቀለብ በተጣበበ ቅጥር ባርነት ቀመስ ህይወት መምራት።
ወደነበርኩበት ለመመለስ የሚጠቅመኝ የእምጰርጵርን ልብ ማለዘብ ብቻ ነው። ነጭ አረቄ ገዝቼ ወደ ቤታቸው ሄድኩ።
ወደውስጥ ስዘልቅ የልጅ ልጆቻቸውን እስከ ምንጅላት እያስቆጠሩ ነበር።
"ዋ-እናንተ ልጆች" ይላሉ። እኔን ሲያዩ ችላ እንደማለት ብለው በቁመት እጅግም ወደማይበልጧቸው ልጆች አተኮሩ።
"እንደምን አደራችሁ?" እንደአዲስ ገቢ ድምፄን ከፍ አድርጌ።
"እኝደምን አደርክ?" ብለው በኩርፊያ ፊታቸውን አዙረው "መቼ ክንብንብህ ተገለጠ?"
"የምን ክንብንብ?"
"ቤትህ ስመጣ ተከናንበህ ላየህ ለአመትም የምትገለጥ አይመስልም ነበር። " ናዳ መጣብህ ቢሉት ተከናንቤአለሁ"እንዳለው ሰው መሆኑ ነው። መቼም ናዳን ክንብንብ እንደማይገታው የቄስ ልጅ ነህና ላንተ አልጠልጥም።"
አሁንም ሰደቡኝ። ምን ይሆናል? ፈገግ አልኩ የግዴታ ፈገግታ።


"ምን እግር ጣለህ?"
"ይቺን መርቀው ቢከፍቱና እየቀመስን ብንጨዋወት ብዬ ነው።" በብብቻዬ የያዝኩትን በጋዜጣ የተጠቀለለ አረቄ ጠረጴዛ ላይ ጎለትኩት። አረቄውን በማየት ብቻ ዘና አሉ። ምልክትነቱ ይቅርታ ያድርጉልኝ የሚል መሸነፍ እንደሆነ አላጡትምና።
"በደህና ጊዜ ቢሆን ጥሩ ነበር። አንተ ግን ሲያዝሉትነካሽ፥ ሲያወርዱት አልቃሽ ሆነህብኛል" ብለው የጨው አመድ የመሳሰሉ የልጅ ልጆቻቸው ላይ አፈጠጡ "ወደጓዳ አትገቡም ወይ? አዋቂ ሲያወራ" እየተደነቃቀፉ ገቡ።
አረቄውን አንስተው ጋዜጣውን እንደ መጋረጃ ገለጥ አድርገው አዩ።።
"ኽ-ከ-ከ-ከ- የፈረንጁ ነውና። እንደጥፋትህ ሰንጋ መጣል ይገባህ ነበር። ግን ምን ይሆናል እራስህ ቆርቁሮህ ስትመጣ ባዶ እጅህንም ቢሆን ሁለተኛ ነገር ነው።"
ተቅለሰለስኩ።
አረቄውን ይዘው ቆሙ። እኔም ቆምኩ። መክደኛውን በቀኝ እጃቸው እየጠመዘዙ፦
"የአብርሃምና የሳራን ነጭ አረቄ የባረከ የእኛንም ይባርክ" አሉ።
ሳቄ መጣ። እራሴን ተቆጣሁት።
ለዚህም አማቻችን ልብ ስጠው የሚደባደብበት ቀልብ ስጠው አማቱን የሚፈራበት፣ ዘር ስጠው፣ ትዳሩን አጥብቆ የሚይዝበት።" ጨረሱና በክዳኑ ቀመሱ።
***
ቁርስ ሳንበላ ስለተያያዝነው ገና ሁለት መለኪያ እንደቀነደብን ሞቅ አለን። ሞቅታ ደጉ በክብር እሳቸው ዝቅ እኔ ከፍ ያሉ ይመስል ትክክልነት ሰፈነብን።
እንዲረሳሳ የምፈልገውን ጉዳይ አነሳሁ።
በሞቅታ "ያንዬ ስለጆቢራ እና ስለርስዎ አባት ያነሳሁት እጎዳ ብዬ ሳይሆን ለወግ መነሻ እንዲሆነን ነበር።"
ሞያ በሚገፍ ሞቅ ያለ እይታ ቆዩብኝና "መች አጣሁት" አሉ።
ሞቅታዬ ልትበር ካቆበቆበች በኋላ እየተረጋጋች "እውነት?" አልኳቸው።
"ኋላ ውሸት ነው? ሰማህ ወይ። ከነተረቱ'ኮ የሚባለው የአርበኛ ልጅ ይወጋል፥ የአሮጌ ልጅ ያወጋል'ም አይደል?"
በነገር ወጋጉኝ። ግልፍ ሊለኝ ካለ በኋላ ያለሁበትን አስታውሼ ተውኩት።
ወሪሳ
አለማየሁ ገላጋይ
ክገጽ 152_154

Comments


bottom of page