top of page

ፈተና

Writer: Ethiopian WritersEthiopian Writers

Updated: May 4, 2024

ከደራሲ ቴዎድሮስ አበበ


ጊዜው ይሆን?

ይህ ዘመነ ጥርጥር

ይህ ዘመነ ክሕደት ይህ ዘመነ ክፍፍል

ይህ ዘመነ ሽንፈት

ይህ ዘመነ ብሶት

ይህ ዘመነ ሽሽት ይህ ዘመነ ግዞት

ይህ ዘመነ ድለላ ይህ ዘመነ እጦት

ጊዜው ይሆን?

እኛ ላይ መስፈር መግነኑ

ማንነታችንን ማምከኑ

ጽናታችንን ማቅጠኑ

ማስተዋላችንን መሸፈኑ

  ፈተና
ከደራሲ ቴዎድሮስ አበበ

ጊዜው ይሆን?

የዐይኖቻችን መዘጋት

የልቡናችን መደፈን የመሠረታችን መናጋት

የውርሳችን መነቀፍ የታሪካችን መወጋት

የዓላማችን መሸርሸር የእምነታችን መጠቃት

ጊዜው ይሆን?

የማዕበሉ ማየል የንዳዱ መበርታት

የፈተናው መክበድ የመሰናክሉ መብዛት

የደጀንነታችን መዳከም የኑፋቄው መራባት

የክሕደት ምላሶች መርዘምና መዘርጋት

ጊዜው ይሆን?

ወይስ እኛው እንሆን ጊዜውን ያበቀልነው?

ዘርተን ኮትኩተን ተንከባክበን በዝምታችን ያሳደግነው

እኛው እንሆን?

ጋሻችንን ጥለን

አጥራችንን አላልተን

በራችንን አስፍተን

የመጤን ወረራ አደጋውን አቃለን

ሲከፋም _ _ _

የራሳችንን ንቀን

ለውጭ ፍልስፍና ሰግደን

ለባዕድ እምነት አጎብድደን

ዘመናዊነትን ፍለጋ ከራሳችን ጋር ተጣልተን

ከራሳችን ተኳርፈን

የራሳችንን ተጠይፈን

በራሳችን ላይ አድመን

እኛው እንሆን?

ዘመኑን የፈጠርነው

ጊዜውን የረዳነው

ማንነታችንን ለማደስ ማንነታችንን የፋቅነው

ጥፋቱን ያከፋነው

ውድቀታችንን ያፋጠንነው

አደራችንን ያልጠበቅነው

ጊዜው ነው ወይስ እኛ?

እኛ።

___________________________________

የካቲት 1997 ዓ ም፤ February 2005

"ፈተና የእንባ ጉዞዎች"

ገጽ 70

ከቴዎድሮስ አበበ የግጥም መጽሐፍ የተወሰደ


Comments


  • Facebook
  • Instagram
  • Twitter
bottom of page